ይህ መረጃ ለመመሪያ ብቻ እንዲሆን እንጂ የህግ ባለሞያ ምክርን ተክቶ መጠቀም ኣይቻልም።

የኪራይ ጭማሪዎች

በአከራይ ተከራይ ስምምነቱ (አንዳንድ ጊዜ “የኪራይ ውል” ተብሎ ይጠቀሳል) ዘመን ውስጥ አከራዩ የኪራዩን መጠን ለመጨመር ቢፈልግ ተገቢውን ማስታወቂያ መስጠት የሚኖርበት ሲሆን የሚጨመረው የኪራይ መጠን ከመቼ ጊዜ ጀምሮ እና ምን ያህል መሆን እንዳለበት የተወሰኑ ገደቦች አሉበት፡፡

ኪራይ ለመጨመር ይቻላልን?

በስምምነቱ ውስጥ በግልፅ በጽሁፍ ካልተመለከተ በስተቀር የኪራይ ስምምነቱ ጸንቶ የሚቆይበት ጊዜ የተገደበ ከሆነ የኪራዩን የዋጋ መጠን ለመጨመር አይቻልም፡፡   እንዳለመታደል ሆኖ ብዙዎቹ የአከራይ ተከራይ ስምምነቶች በሪል ኢስቴት ወኪሎች የሚዘጋጁ በመሆኑ እነዚህን ድንጋጌዎች ይይዛሉ፤ በመሆኑም ስምምነቱን ከመፈረምዎ በፊት በጥንቃቄ ማንበብ አስፈላጊ ነው፡፡  በተለይም የኪራይ ጭማሪዎች ለሁሉም ስምምነቶች እንደጠቃሚ መምሪያ ተደርጎ በሚዘጋጀው በመደበኛው ድንጋጌ ውስጥ የማይካተቱ በመሆኑ በስምምነቱ ውስጥ በተካተተው በዚህ ድንጋጌ የማይስማሙ ከሆነ እንዲሰረዝ ለመደራደር መብት አለዎት፡፡     አከራዩ እንደጠቃሚ መምሪያ ተደርጎ በሚዘጋጀው በመደበኛው ድንጋጌ ውስጥ በማይካተቱት በእነዚህ ድንጋጌዎች ላይ ለመደራደር ፈቃደኛ ካልሆነ ስምምነትዎ በተጠቃሚዎች ሕግ መሠረት ሚዛናዊነት የጎደለው ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡

ማሳሰቢያ፡ እርስዎና አከራዩ ድንጋጌው ከስምምነቱ ላይ በቀለም ምልክት መሰረዙ እንዲመለከት ከተስማማችሁ ሁለታችሁም በዚሁ መስማማታችሁን ለማሳወቅ ከተሰረዘው ድንጋጌ አጠገብ ፊረማችሁን ማስቀመጥ ይኖርባችኋል፡፡

በምን ያህል ድግግሞሽ ነው ኪራይ መጨመር የሚኖርበት?

እ.ኤ.አ. በጁን 19 ቀን 2019 ወይም ከዚህ ቀን በኋላ በጊዜ የተወሰነ የኪራይ ስምምነት ፈጽመው ከሆነ በ12 ወራት ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ የኪራይ ጭማሪ ሊደረግብዎት አይቻልም፡፡

እ.ኤ.አ. ከጁን 19 ቀን 2019 በፊት በጊዜ የተወሰነ የኪራይ ስምምነት ፈጽመው ከሆነ በ6 ወራት ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ የኪራይ ጭማሪ ሊደረግብዎት አይቻልም፡፡ ይሁንና እ.ኤ.አ. ከጁን 19 ቀን 2019 በፊት የገቡት በጊዜ የተወሰነ የኪራይ ስምምነት ካበቃና የኪራዩ ስምምነት በየወቅቱ ወደሚደረግ ስምምነት ከተቀየረ የኪራይ ጭማሪው ድግግሞሽ በ12 ወራት ውስጥ ወደ አንድ ጊዜ ይቀየራል፡፡ እ.ኤ.አ. ከጁን 19 ቀን 2019 በፊት የገቡት የኪራይ ስምምነት በየወቅቱ የሚደረግ ከነበረና እ.ኤ.አ. በጁን 19 ቀን 2019 ወይም ከዚህ ቀን በኋላ አዲስ በጊዜ የተወሰነ የኪራይ ስምምነት ከፈረሙ ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ በተመሳሳይ የሚፈጸም ነው፡፡

በየወቅቱ የሚፈጸም የኪራይ ስምምነት (ለምሳሌ ከወር ወደ ወር የሚደረግ) ከሆነ እና በጊዜ የተወሰነ የኪራይ ስምምነት ሆኖ በስምምነቱ ውስጥ የኪራይ ጭማሪ የሚፈቀድ ከሆነ አግባብነት ያላቸው የድግግሞሽ ጊዜዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ (በገቡት በጊዜ የተወሰነ የኪራይ ስምምነት ውስጥ አግባብነት ባለው የድግግሞሽ ጊዜ ወቅት ከአንድ ጊዜ በላይ የኪራይ ጭማሪ የሚፈቅድ ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡)

የኪራይ ጭማሪ ማስታወቂያ

አከራዩ ጭማሪ ከማድረጉ በፊት በጽሁፍ የ60 ቀን ማስታወቂያ ሊሰጥዎት የሚገባ ሲሆን ጭማሪው ከተገቢው በላይ ነው ብለው የሚያምኑ ከሆነ ጭማሪው እንዲመረመርልዎት ለኮንሲዩመር አፌይርስ ቪክቶሪያ (CAV) የማመልከት መብት ያለዎት መሆኑን የሚገልጽ ተገቢውን ቅጽ መጠቀም ይኖርበታል፡፡    ማስታወቂያው የሚያገለግለው ለአንድ የኪራይ ጭማሪ ብቻ ነው፡፡

የኪራይ ጭማሪ ማስታወቂያው እነዚህን ሁሉ ሁኔታዎች የማያሟላ ከሆነ ተፈጻሚነት የማይኖረው ከመሆኑም በላይ የተጨመረውን መጠን ለመክፈል አይገደዱም፡፡ የኪራይ ጭማሪ የተደረገ መሆኑን የሚገልጽ ማስታወቂያ ከደረሰዎትና ማስታወቂያው ተፈጸሚነት የማይኖረው ነው ብለው የሚያምኑ ከሆነ ምክር ለማግኘት እኛን፣   የአካባቢዎን TAAP አገልግሎትን፣ , የቴናንሲ ፕላስ   ፕሮቫይደርን ወይም  የኮሚዩኒቲ ሌጋል ሲንተርን  ያግኙ፡፡

ማስታወቂያ ስለመስጠት

የኪራይ ጭማሪ ማስታወቂያ ለእርስዎ በአካል፣ በፖስታ፣ ወይም ስምምነት ካላችሁ እንደ ኢሜይል ባለ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ ሊደርስዎት ይገባል፡፡ ማስታወቂያው በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ከተላከልዎትና በዚህ መንገድ እንዲፈጸም ፈቃድዎን ያልሰጡ ከሆነ ውልዎን ይመልከቱና ለተጨማሪ ምክር እኛን ያግኙን፡፡
ማስታወቂያው የተላከው በፖስታ ከሆነ አከራዩ ፖስታው እስኪደርስዎት በቂ ጊዜ ሊሰጥዎት ይገባል፡፡ በአውስትራሊያ የፖስታ ማድረሻ ጊዜን ይመልከቱ፡፡.

የኪራይ ጭማሪን ስለመቃወም

የኪራይ ጭማሪው እጅግ ከፍተኛ ነው ብለው የሚያስቡ ከሆነ የኮንሲዩመር አፌይርስ ቪክቶሪያ ኢንስፔክተር መጥቶ ንብረቱን ተመልክቶ ጭማሪው ምክንያታዊ ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑ እንዲወስን ለመጠየቅ ይችላሉ፡፡ ጥያቄውን ማስታወቂያው በደረሰዎት በ30 ቀናት ውስጥ ማቅረብ ይኖርብዎታል፡፡

ጥያቄውን የሚያቀርቡትም ለ፡
The Director Consumer Affairs Victoria
GPO Box 123
Melbourne VIC 3001
ወይም በኢሜይል፡ renting@justice.vic.gov.au
ወይም በፋክስ፡ 8684 6310

ተቆጣጣሪው የንብረቱን ሁኔታ፣ ፋሲሊቲዎችን፣ እና ከንብረቱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አገልግሎቶች መመልከትና በማስታወቂያው ላይ የተመለከተውን የኪራይ መጠን በአካባቢው ከሚገኙ ተመሳሳይ ንብረቶች ጋራ ማነጻጸር ይኖርበታል፡፡ ምርመራው በሚካሄድበት ወቅት ጭማሪው ከፍተኛ ነው በማለት ያቀረቡትን ተቃውሞ የሚደግፍልዎትን ማናቸውም ነጥብ መግለጽ ይኖርብዎታል፡፡ ይህም የሚያካትተው፡

  •  ንብረቱ ምን ያህል ጥገና የተደረገለት ስለመሆኑ
  •  በአካባቢው ላይ ያሉ ችግሮች
  •  በአካባቢው ላይ የሚገኙ ንብረቶች በምን ያህል ዋጋ የሚከራዩ ስለመሆኑ
  • በአከራዩ መቅረብ ሲገባቸው በእርስዎ አማካይነት የሚያቀርቧቸው ፋሲሊቲዎች ወይም አገልግሎቶች
  •   በአከራዩ ፈቃድ ወይም ስምምነት በቤቱ ላይ የሰሩት ሥራ ካለ
  •  ስምምነታችሁን ከፈጸማችሁ ወዲህ ወይም ባለፈው ጊዜ የኪራይ ጭማሪ ከተደረገ ወዲህ በኪራዩ ላይ የተደረገ ለውጥ እና በንብረቱና በፋሲሊቲዎቹ ላይ ያለው ሁኔታ
  •  ባለፉት 24 ወራት ውስጥ የተደረጉ የቤት ኪራይ ጭማሪዎች (ካለ) ብዛት እና በእያንዳንዱ ጭማሪ ላይ የጭማሪው መጠን

እርስዎ ኢንስፔክተሩ ጭማሪውን እንዲመረምርልዎ ጠይቀው ከሆነ በጭማሪው ላይ የሚያደርጉትን ምርመራ ካጠናቀቁ በኋላ በጭማሪው ላይ ያላቸውን አስተያየት ለእርስዎና ለአከራዩ በጽሁፍ ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ ኢንስፔክተሩ ጭማሪው የተጋነነ ነው ብሎ ካመነ ከአከራዩ ወይም ከሪል ኢስቴቱ ወኪል ጋር ተገቢ ነው ብለው በሚያምኑት ዋጋ ላይ ድርድር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

ሁለቱ ወገኖች ድርድሩን ማድረግ ካልቻሉ ወይም መስማማት ካልቻሉ እርስዎ ሪፖርቱን ካገኙ በኋላ ጭማሪው እንዳይፈቀድ ትዕዛዝ እንዲሰጥልዎ ለቪክቶሪያ ሲቪል ኤንድ አድሚኒስትሬቲቭ ትራይቡናል (VCAT) ማመልከት ይችላሉ፡፡ የኢንስፔክተሩ ሪፖርት በደረሰዎት በ30 ቀናት ውስጥ ማመልከት ይኖርብዎታል፡፡

የቪክቶሪያ ሲቪል ኤንድ አድሚኒስትሬቲቭ ትራይቡናል (VCAT) ጭማሪው የተጋነነ ነው ብሎ ካመነ ጭማሪው እንዳይደረግ ወይም በአነስተኛ መጠን እንዲጨምር ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እንዲሁም አከራዩ ኪራይ ሊጨምር የማይችልበትን ጊዜ (እስከ 12 ወራት) ሊያስቀምጥ ይችላል፡፡ ይሁንና VCAT እነዚህን ትዕዛዞች ሊሰጥ የሚችለው ጭማሪው የቤቱን ኪራይ መጠን በአካባቢው ከሚገኙ ተመሣሣይ ንብረቶች ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ አድርጎት ሲያገኘው ነው፡፡

VCAT ጉዳይዎን ማየት ከመጀመሩ በፊት የዋጋ ጭማሪው ሥራ ላይ መዋል የጀመረ ከሆነ VCAT በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ጭማሪውን መክፈል ይኖርብዎታል፡፡ ለእርስዎ የሚወሰነልዎት ከሆነ የከፈሉትን ጭማሪ ክፍያ አከራዩ እንዲመልስልዎት VCAT ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡

የአገልግሎቶች ወይም ፋሲሊቲዎች መቀነስ

አከራዩ የቤት ኪራዩን ዋጋ ሳይቀንስ ከንብረቱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አገልግሎቶች ወይም ፋሲሊቲዎች ከቀነሰ (ለምሣሌ የጋራ የልብስ ማጠቢያውን ከዘጋ) የኪራይ ቅናሽ ሊደረግልዎት ይገባ እንደሆነ ከኮንሲዩመር አፌይርስ ቪክቶሪያ ሪፖርት ለመጠየቅ ይችላሉ፡፡ ሪፖርቱ እርስዎን የሚደግፍ ከሆነ የኪራይ ቅናሽ እንዲደረግ ትዕዛዝ እንዲሰጥልዎ ለVCAT ማመልከት ይችላሉ፡፡ የኢንስፔክተሩ ሪፖርት በደረሰዎት በ30 ቀናት ውስጥ ለVCAT ማመልከት ይኖርብዎታል፡፡

ከአከራይ ጋር ስለሚደረግ ድርድር

በቀረበ የኪራይ ጭማሪ ሃሳብ ላይ ከአከራዩ ጋር ወይም ከሪል ኢስቴቱ ወኪል ጋር ድርድር ለማድረግ መሞከር ጠቃሚ ነው፡፡
በተለይ በቤቱ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆዩና እምነት የሚጣልብዎት ተከራይ ከሆኑ ወይም በጭማሪው ምክንያት ቤቱን ለመልቀቅ የሚገደዱ ከሆነ ጭማሪውን ሊቀንሱልዎት ይችላሉ፡፡

የኢንስፔክተር ሪፖርት በእጅዎ ላይ ካለ ወደVCAT ከመሄድዎ በፊት ከአከራዩ ወይም ከወኪሉ ጋር ለመደራደር ሪፖርቱን መጠቀም ይችላሉ፡፡   የሚያደርጉት ማናቸውም ስምምነት በጽሁፍ ሆኖ በእርስዎ በራስዎና በአከራዩ ወይም በወኪሉ መፈረሙንና የስምምነቱ ቅጂ የደረስዎት መሆኑን ያረጋግጡ፡፡

ጭማሪውን ለመክፈል ፈቃደኛ አለመሆን

አከራዩ ወይም ወኪሉ ሕጋዊ አግባብ ያለው የቤት ኪራይ ጭማሪ ማስታወቂያ ቢሰጡዎትና እርስዎ ለመክፈል ፈቃደኛ ባይሆኑ ውዝፍ ዕዳ ውስጥ ይገባሉ (ማለትም ኪራይዎን እንዳልክፈሉ እንደመቆጠር)፡፡ ይህም ደረጃ በደረጃ ያልተከፈለ የ14 ቀን ኪራይ ቢሆንና የ14 ቀን ውዝፍ ቢኖርብዎ አከራዩ ወይም ወኪሉ ቤቱን እንዲለቁ የ14 ቀን ማስታወቂያ ሊሰጡዎትና ተገደው ከቤቱ እንዲወጡ እንዲደረግ ለVCAT ማመልከት ይችላሉ፡፡ የእርስዎን ሃሳብ እንዲያቀርቡ ለማድረግ ዕድል ይሰጥዎታል፤ ነገር ግን ተገደው ከቤቱ እንዲለቁ ሊደረግም ይችላል፡፡

ይህ መረጃ ለመመሪያ ብቻ እንዲሆን እንጂ የህግ ባለሞያ ምክርን ተክቶ መጠቀም ኣይቻልም።


[disclaimer-rta-amharic]

ተዛማጅ ገፆች

 የኪራይ ውዝፎች 

ሕጉ

Residential Tenancies Act 1997 (AustLII website)

Section 44 –ምን ያህል የኪራይ ጭማሪ ማስታወቂያ ነው የሚያስፈልገው ?

ክፍል 45 – ተከራይ ስለ ኪራይ አቤቱታ ለ CAV ቅሬታ ሊያቀርብ ይችላል

 ስለተደረገ ከፍተኛ ጭማሪ ለVCAT ስለማመልከት 

ክፍል 47 -VCAT ምን ዓይነት ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል ?

ክፍል 48 – VCAT ኪራዩ ተመላሽ እንዲደረግ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል 

ክፍል 506 – የሰነዶች አገልግሎት

Was this page helpful?

Cookies and Privacy:This site uses cookies to ensure you get the best experience on our website.

Find out more Accept