ይህ መረጃ ለመመሪያ ብቻ እንዲሆን እንጂ የህግ ባለሞያ ምክርን ተክቶ መጠቀም ኣይቻልም።

የኪራይ ውልን ማፍረስ

የቋሚ ጊዜ የኪራይ ውል (አብዛኛውን ጊዜ ኪራይ የሚባለው) ካለዎትና የዚህ ቋሚ የኪራይ ዘመን ከማብቃቱ በፊት ቤቱን ለቅቀው መውጣት ከፈለጉ ከፈለጉ ከዚህ በሚከተሉት ሁኔታዎች ውሉን ለማቋጥ ይችላሉ፡ አንዳንድ የውል ማቋረጫ መንገዶች ወጪ የሚያስከትሉብዎ ሊሆኑ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

የጋራ ስምምነት

ማናቸውም የኪራይ ውል ስምምነት በአከራዩ እና በተከራዩ መካከል በሚደረግ ‘የጋራ ስምምነት’ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ስምምነቱን በጽሁፍ እንዲያሰፍሩትና የውሉ በዚህ መንገድ መፍረስ በእርስዎ ላይ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ወጪ ወይም የካሣ ክፍያ እንደማያስከትልብዎ በስምምነቱ ውስጥ መገለጹን እንዲያረጋግጡ አበክረን እንመክራለን፡፡ እርስዎ እና አከራዩ በስምምነቱ ላይ ፊርማችሁን ማኖር ይኖርባችኋል፡፡ የስምምነቱን አንድ ቅጂ ለእርስዎ ማስቀረትዎን ያረጋግጡ፡፡

አከራይ ውሉን በሚጥስበት ወቅት

አከራይዎ በResidential Tenancies Act 1997ሥር የተመለከቱትን ግዴታዎቹን ከጣሰ እርስዎ የኪራይ ውሉ ዘመን ከማብቃቱ በፊት ውሉን ማቋረጥ ይችላሉ፡፡ ይህም ተፈጻሚ የሚሆነው አከራዩ፡

 • እርስዎ ወደ ተከራዩት ቤት ለመግባት በሚዘጋጁበት ወቅት አከራዩ ቤቱን በሚገባ አኳኋን ንጹህ እና ባዶ መሆኑን ካላረጋገጠ
 • በቤቱ ‘በሰላምና በጸጥታ’ የሚኖሩበትን ሁኔታ ካላረጋገጠ
 • ቤቱን በጥሩ ሁኔታ ካላደሰው
 • የውጭ በሮች እና መስኮቶች ተዘግተው የሚጠበቁበትን ቁልፎች ካልሰጠዎት፣ ወይም ቁልፎቹን በሚቀይርበት ወቅት እነዚህን የተቀየሩ ቁልፎች ካልሰጠዎት
 • የተበላሹ የቧንቧ ውሃ መሣሪያዎችን ከፍተኛ ጥራት ባላቸው መሣሪያዎች ካልቀየራቸው

 

ከላይ ከተጠቀሱት ከአከራዩ የውል ጥሰት ምክንያቶች ውስጥ በአንዱ የኪራይ ውልዎን ለማቋረጥ ከፈለጉ ሊከተሏቸው የሚገቡ ደረጃዎች አሉ፡፡

 1. ማድረግ ከሚገባዎት ውስጥ አንደኛው አከራዩ በ14 ቀናት ውስጥ ችግሩን እንዲያርም (እንደ አግባብነቱ ካሣ እንዲከፍልዎት) ለማሳሰብ የውል ጥሰት ማስታወቂያ መላክ ነው፡፡
 2. አከራዩ ይህን መፈጸም ካልቻለ የማስፈጸሚያ ትዕዛዝ እንዲያወጣልዎት ለ Victorian Civil and Administrative Tribunal ማመልከት ይችላሉ፡፡
 3. አከራዩ በማስፈጸሚያ ትዕዛዙ መሠረት ካልፈጸመ ቤቱን በ14 ቀናት ውስጥ ለቅቀው ለመውጣት እንደሚፈልጉ የሚገልጽ ማስታወቂያ ሊልኩለት ይችላሉ፡፡
 4. እንዲሁም ለአከራዩ ከዚህ ቀደም ለተመሣሣይ ጥፋት ሁለት ጊዜ የውል ጥሰት ማስታወቂያ ልከውለት ከነበረና አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ ይህንኑ ግዴታውን ከጣሰ ቤቱን በ14 ቀናት ውስጥ ለቅቀው ለመውጣት እንደሚፈልጉ የሚገልጽ ማስታወቂያ ሊልኩለት ይችላሉ፡፡

ለሌላ ማስተላለፍ

ውልዎን በማፍረስ ፋንታ የኪራይ ስምምነትዎን ለሌላ ተከራይ አሳልፎ መስጠት ወይም ማስተላለፍ ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡  ሆኖም ይህን ለማደረግ የአከራይዎን ስምምነት ማግኘት፣ የኪራይ ውሉን ማሻሻል፣ እና አዲሱ ተከራይ ለሚያጠፋው ተጠያቂ እንዳይሆኑ መያዣዎ በአዲሱ ተከራይ እንዲቀየር ማድረግ ስላለብዎ ይህ አማራጭ ቀላል አማራጭ አይደለም፡፡ እንዲሁም አከራዩ ለሌላ ማስተላለፉን በጽሁፍ ስለሚያዘጋጅ ላወጣው ወጭ ተመጣጣኝ ክፍያ ሊጠይቅዎት የሚችል ቢሆንም ከአዲሱ ተከራይ ጋር የሚያደርገውን የኪራይ ስምምነት ለማዘጋጀት ላወጣው ወጪ ሊጠይቅዎት አይችልም፡፡

ችግር

አንድ ያልታሰበ ነገር ቢያጋጥምዎትና በዚህም ምክንያት በጊዜ የተወሰነው የኪራይ ዘመን እስከሚያበቃ ድረስ ለመቆየት ከፍተኛ ችግር የሚያስከትልብዎ ቢሆን ይህ በጊዜ የተወሰነው የኪራይ ዘመን እንዲቀነስልዎትና የኪራ ውሉን ለማቋረጥ እንዲፈቅድልዎ ለ Victorian Civil and Administrative Tribunal ማመልከት ይችላሉ፡፡ ፍርድ ቤቱ በተቻለ ፍጥነት ጉዳይዎን እንዲያይልዎ ለመጠየቅ ይችላሉ፡፡ ጉዳይዎ መታየት እስኪጀምር ድረስ የቤት ኪራይዎን መክፈል ይኖርብዎታል፡፡ ችግር እንዳጋጠምዎ ማመልከት ከፈለጉ ማመልከቻዎን ከቤቱ ከመውጣትዎ በፊት ማስገባት ይገባዎታል፡፡

ችግር አጋጥሞኛል በማለት ለማመልከት ለፍርድ ቤቱ የሚከተሉትን ማረጋገጥ ይኖርብዎታል፡

 • በእርስዎ ኑሮ ያልተጠበቀ ለውጥ ያጋጠመዎት (ለምሣሌ ከሥራዎ ተሰናብተዋል) መሆኑን እና የቤት ኪራይ ግንኙነቱ የሚቀጥል ከሆነ ከፍ ያለ ቸግር የሚደርስብዎ መሀኑን፤ እና
 • የቤት ኪራይ ውሉ ካልተቋረጠ በእርስዎ ላይ የሚደርሰው ጉዳት የኪራይ ውሉ ቢቋረጥ በአከራዩ ላይ ከሚደርሰው ጉዳት የበለጠ መሆኑን

 

በችግር ምክንያት የቤት ኪራይ ውሉን በሚያቋርጡበት ወቅት አከራዩን መካስ ሊያስፈልግዎት ይችላል (ወጭዎች የሚለውን ይመልከቱ)፡፡

ችግር እና የቤተሰብ ሁከት

በቤተሰብ ሁከት የጣልቃ ገብነት ትዕዛዝ መሠረት ‘የተጠበቀ ሰው’ ከሆኑ እና እራስዎን ወይም ልጆችዎን ለመከላከል በመፈለግ ከቤቱ መውጣት ካስፈለገዎ በጊዜ የተወሰነው የኪራይ ውልዎ እንዲቀነስና በችግር ምክንያት የኪራይ ውሉ እንዲቋረጥ ለፍርድ ቤቱ ማመልከት ይችላሉ፡፡

በቤተሰብ ሁከት ትዕዛዝ ምክንያት ከኪራይ ቤት እንዲወጡ ከተደረጉ በጊዜ የተወሰነው የኪራይ ውልዎ እንዲቀነስና በችግር ምክንያት የኪራይ ውሉ ቀደም ብሎ እንዲቋረጥ ለፍርድ ቤቱ ማመልከት ይችላሉ፡፡

ንብረትን አሳልፎ መስጠት

ከላይ የተጠቀሱት የኪራይ ውል ማቋረጫ መንገዶች ጥሩ አማራጭ ካልሆኑልዎት ንብረቱን አሳልፎ በመስጠት በጊዜ የተወሰነውን የኪራይ ውል ቀደም አድርገው ለማቋረጥ ይችላሉ፡፡  አብዛኛውን ጊዜ ይህ የሚሆነው ቤቱን የሚለቁ መሆኑን የሚገልጽ ማስታወቂያ ለአከራዩ በመስጠት (ለምሣሌ ቤት ለመልቀቅ ስለመፈለግ የሚሰጥ ማስታወቂያ) እና ቤቱን ለቅቀው ሲወጡ የቤቱን ቁልፍ መልሰው በመስጠት ነው፡፡

ወጭዎች

በችግር ምክንያት ወይም ንብረቱን መልሶ በመስጠት የቤት ኪራይ ውልን ማፍረስ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡   ውልዎን በማፍረስዎ ምክንያት አከራዩ ላወጣው አግባብነት ያለው ወይም ምክንያታዊ ወጭዎች ካሣ እንዲከፈሉት ሊጠይቅ ይችላል፡፡

እርስዎ እንዲከፍሉ የሚጠየቁት ወጭ የሚከተሉትን ይጨምራል፡

 • እንደገና ለማከራየት የሚደረግ ክፍያ (አብዛኛውን ጊዜ የአንድ ወይም የሁለት ሣምንት ኪራይ)፡፡ ይህ የሚመሰረተው ወኪሉ አከራዩን በጠየቀው ክፍያ ላይ በመሆኑ ሂሳብ የተጠየቀበትን ኢንቮይስ ቅጂ መጠየቅ ይመከራል፡፡
 • ምክንያታዊ የማስታወቂያ ወጪዎች
 • አዲሱ ተከራይ እስኪገባ ድረስ ወይም በጊዜ የተወሰነው የኪራይ ዘመን እንሰከሚያበቃ የሚኖር የኪራይ ዋጋ (ከሁለት አንዱ ቀድሞ የሚፈጸመው)፡፡

 

አከራዩ ወይም ወኪሉ የማይነግሩዎት ነገር ቢኖር ቤቱ እንደገና እስከሚከራይ ወይም የማስታወቂያ ክፍያዎች መክፈል የሚኖርብዎት በሚዛናዊ ምደባ ላይ የተመሰረቱ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ማለት እርስዎ እነዚህን ክፍያዎች መክፈል የሚኖርብዎት አከራዩ የኪራይ ክፍያ ላልተቀበለበት ቀሪ የኪራይ ዘመን ብቻ ነው፡፡ ለምሣሌ የ12 ወራት በጊዜ የተወሰነ ውል ቢኖርዎትና 7 ወራት ከኖሩ በኋላ ቤቱን ቢለቁ የቀረዎት የኪራይ ዘመን 40% በመሆኑ ብቻ በመሆኑ እንዲከፍሉ የሚጠበቅብዎት ቤቱ እንደገና እስከሚከራይ ወይም የማስታወቂያ ክፍያዎችን 40% ብቻ ነው ማለት ነው፡፡

ወጪዎቹን ማስተዳደር

የኪራይ ውሉን ማቋረጥ ከፈለጉ በሚቻለው መጠን ማስታወቂያ መስጠት ይኖርብዎታል (የደብዳቤዎን ቅጂ ይያዙ)፡፡ ቤቱን የሚለቁበትን ትክክለኛ ቀን መግለጽ እና አከራዩ ወይም ወኪሉ ሌላ ተከራይ እንዲፈልጉ መግለጽ ጥሩ ነው፡፡ ኣከራዩ በተቻለ ፍጥነት አዲስ ተከራይ ለማግኘት ሁሉንም ተገቢ እርምጃዎችን ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡ አዲስ ተከራይ እንዲገኝ ለመርዳት (ለምሣሌ ቤቱን ለማሳየት በመተባበር ወይም ቤቱን እራስዎ በማስተዋወቅ) በሞከሩ ቁጥር የሚከፍሉበትን ሁኔታ ለመቀነስ ያስችለዎታል፡፡

የቤት ኪራዩን የሚከፍሉት ቤቱን እስከሚለቁበት ቀን ድረስ ያለውን ብቻ ነው፡፡ አዲሱ ተከራይ ወደ ቤቱ ከገባ እርስዎ ለአከራዩ የሚከፍሉት አከራዩ ያጣውን የኪራይ ዋጋ ካሣ ብቻ ነው፡፡

እርስዎ ማስታወቂያ ከሰጧቸው ቀን ጀምሮ አከራዩ ወይም ወኪሉ ቤቱን እንደገና ለማከራየት ተገቢውን ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑ መከታተል የሚኖርብዎት ሲሆን አዲሱ ተከራይ ወደ ቤቱ የገባበትንም ቀን አረጋግጠው ይያዙ፡፡ አከራዩ የሚደርስበትን የወጪ ጉዳት ለመቀነስ ሃላፊነት የሚኖርበት ሲሆን አዲስ ተከራይ ለማግኘት ያለውን ዕድል የሚያጠብ ከሆነ (ለምሣሌ የቤቱን ኪራይ ዋጋ ከፍ በማድረግ) ወይም አዲስ ተከራይ ለማግኘት ጥረት የማያደርግ ከሆነ ሙሉውን የካሣ ክፍያ ማድረግ የለብኝም ብለው መከራከር ይችላሉ፡፡

በዋናው ጋዜጦች እና በኪራይ ዝርዝሮች ውስጥ ከ ‘ወኪል’ የሚገኘውን ‘ለመልቀቅ የሚረዱ ንብረቶች’ ክፍልን ይመልከቱ ፡፡ ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ከሆነ የወኪሉን ዌብ ሣይት መመልከትም ይችላሉ፡፡ ቤቱ እንዲከራይ ማስታወቂያ ያልወጣለት ከሆነ ወይም የሚተዋወቀው በተጋነነ የኪራይ ዋጋ መጠን ከሆነ አከራዩ የሚደርስባቸውን ኪሣራ ለመቀነስ ጥረት ያላደረጉ መሆኑን ሊያሳይ ስለሚችል ይህንን እንደ ማስረጃ መያዝ ይኖርብዎታል፡፡

አከራዩ የሚጠይቅዎት የካሣ ክፍያ ምክንያታዊነት የጎደለው ነው ብለው የሚያስቡ ከሆነ ለመክፈል መስማማት አይኖርብዎትም፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ አከራዩ ካስያዙት መያዣ ላይ እንዲከፈለው ለመጠየቅ ወይም ካሣ እንዲከፈለው ለVictorian Civil and Administrative Tribunal ሊያመለክት ይችላል፡፡ አከራዩ ስላቀረበው የይገባኛል ጥያቄ ማስታወቂያ ሊሰጥዎት የሚገባ ሲሆን እርስዎም ለፍርድ ቤቱ የእርስዎን የመከላከያ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ዕድል ይሰጥዎታል፡፡

ይህ መረጃ ለመመሪያ ብቻ እንዲሆን እንጂ የህግ ባለሞያ ምክርን ተክቶ መጠቀም ኣይቻልም።

[disclaimer-rta-amharic]


 

ለሌላ ማስተላለፍ እና መልሶ ለሌላ ማከራየት
ለአከራይዎ ግዴታን የመጣስ ማስታወቂያ ስለመስጠት
በአከራዩ የሚቀርብ የካሣ ጥያቄን ስላለመቀበል
የኪራይ ግንኙነትን ስለማቋረጥ
የቤተሰብ ውስጥ ሁከት እና ስለ ቤት ኪራይ
ያስያዙትን የመያዣ ገንዘብ መልሶ ስለማግኘት
ከቤቱ ለቅቀው መውጣት ሲፈልጉ

 

Was this page helpful?

Cookies and Privacy:This site uses cookies to ensure you get the best experience on our website.

Find out more Accept